የኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI) እና የናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንሲቱትዩት (NDI) ጥምር የምርጫ ግምገማ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያን የ2013 ምርጫ ዝግጅት አስመልክቶ ያወጣው የቅድመ ምርጫ ምዘና ሪፖርት
በአስቸኳይ የሚሰራጭ፡- ግንቦት 13 ቀን 2021 ዓ.ም.
ለበለጠ መረጃ በሚቀጥለው አድራሻችን ያነጋግሩን፡-
የዋሽንግተን ዲሲ ሚዲያ አድራሻዎች
አይ አር አይ ራያን ማሆኒ: media@iri.org ወይም
በስልክ ቁጥር +1-202-599-7882
ኤን ዲ አይ ክላይተን ማክለስኪ: media@ndi.org
የኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI) እና የናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንሲቱትዩት (NDI) ጥምር የምርጫ ግምገማ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያን የ2013 ምርጫ ዝግጅት አስመልክቶ ያወጣው የቅድመ ምርጫ ምዘና ሪፖርት
ከሚያዚያ 1 እስከ 18 2013 በይነ-መረብ (ኢንተርኔት) በመጠቀም የተከናወነ ከፍተኛ የቅድመ ምርጫ ግምገማ ተልዕኮን ተከትሎ የኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI) እና የናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንሲቱትዩት (NDI) ጥምር የምርጫ ግምገማ ልዑካን ቡድን ግንቦት 28 ቀን 2013 ሊካሄድ በታቀደው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ዝግጅት ላይ ያሰናዱትን የጋራ ሪፖርት ይፋ አድርገዋል።
የኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI) እና የናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንሲቱትዩት (NDI) ጥምር የምርጫ ግምገማ ልዑካን ቡድን በአምባሳደር ጆኒ ካርሰን (የNDI የቦርድ አባል እና የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር)፣ በተከበሩ ኮንስታንስ ቤሪ ኒውማን (የIRI የቦርድ አባል እና የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር)፣ እና በክቡር አህመድ ኢሳክ ሀሰን (የቀድሞው የኬንያ ገለልተኛ ምርጫና ድንበር ኮሚሽን ሊቀመንበር) የተመራ ነው።
ከልዑካን ቡድኑ የማጠቃለያ ግኝቶች እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ምክረ ሃሳቦች የተወሰደ፦ “ግንቦት 28 ይካሄዳል ተብሎ ቀን የተቆረጠልት የኢትዮጵያ የ2013 ምርጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎችን መሠረት በማድረግ በአገሪቱ ውስጥ ሁሉን አቀፍ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችል መልካም ዕድል ሊፈጥር ይችላል የሚል ተስፋ አለ። ሆኖም በስፋት የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን እና የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚከናወኑ የእጩዎች እና የመራጮች ምዝገባ ሥነ-ሥርዓቶች ጋር የተያያዙ መዘግየቶችን፣ አንዳንድ የክልል መንግስታት ደካማ የሆነ ትብብር ማሳየታቸውን፣ ስፊ የህዝብ ድጋፍ ያላቸው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ሂደቱ ራሳቸውን ማግለላቸውን እና እናገላለን የሚል ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን፣ እንዲሁም ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን የህዝብ ጤና ቀውስ ጨምሮ አዳጋች የሆኑ የተለያዩ ጉልህ ችግሮች መኖራቸው መራጮች እና ፓርቲዎች በሂደቱ ውስጥ ለመሳተፍ ባላቸው አቅም ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር እና በዚህም ተዓማኒነት ያለው ምርጫ የመከናወኑን ዕድል እንዳያጠበው ያሰጋል። በመሆኑም ከምርጫ ቀን አስቀድሞ በሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚከወኑ ሁነኛ እና የተቀናጁ ጥረቶች ትርጉም ያለው ምርጫ ለማካሄድ እና ከምርጫው ባሻገር ለብሄራዊ እርቅና ለዴሞክራሲያዊ እድገት መሰረት ለመጣል አስፈላጊ ግብአቶች ናቸው።” (የሪፖርቱ ሙሉ ማጠቃለያ እና ምክረ ሃሳቦች ከዚህ በታች ተያይዘዋል)።
የተከበሩ ኮንስታንስ ቤሪ ኒውማን (የIRI የቦርድ አባል እና የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር) እንዳስረዱት “የኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI) እና የናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንሲቱትዩት (NDI) ጥምር የምርጫ ግምገማ ልዑካን ቡድን ይህንን ትንታኔ ይፋ ሲያደርግ በዓለም አቀፍ ትብብር መንፈስ እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር እና ውጤታማ የምርጫ ልምዶችን ለማጎልበት ለኢትዮጵያ ጥረቶች የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንደሚያደርጉ ተስፋ በማድረግ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎች ተሳትፎን እና ተጠያቂነትን ማሻሻል ይቻላል በሚል ነው።”
አምባሳደር ጆኒ ካርሰን (የNDI የቦርድ አባል እና የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር) ጨምረው እንዳስረዱት “ይህ ምርጫ አዎንታዊ እርምጃ ሊሆን እና ወደ ፊት ይበልጥ ተአማኒነት ያላቸው ሂደቶች እንዲኖሩ መሠረት ሆኖ ሊያገለግል የሚችልበት መልካም ዕድል አለ። የልዑካን ቡድኑ ምርጫው ይፋ በተደረገው መሰረት መከናወኑን የሚደግፉ እንዲሁም የሚቃወሙ አካላትን ሃሳብ አድምጧል። ምርጫው የሚደረግበት ጊዜ መቼም ቢሆን የምርጫውን ድባብ ለማሻሻል የተቀናጁ ጥረቶች ያስፈልጋሉ።”
ክቡር አህመድ ኢሳክ ሀሰን (የቀድሞው የኬንያ ገለልተኛ ምርጫና ድንበር ኮሚሽን ሊቀመንበር) አክለው እንደተናገሩት “እስከ ምርጫ ቀን ድረስ ባለው ውስን ጊዜ ውስጥም ቢሆን የ2013 የኢትዮጵያ ምርጫ እንዲሁም ለወደፊቱ የሚደረጉ ምርጫዎች ሀገሪቱን ወደፊት የሚያራምዱ እንዲሆኑ ለማገዝ ኢትዮጵያውያን ሊወስዷቸው እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፋቸው የሚችሉ ወሳኝ እርምጃዎች አሉ። የዴሞክራሲ መስፋፋትን ለማጎልበት ኢትዮጵያውያን ለሚያደረጓቸው ጥረቶች አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት ተስፋ በማድረግ፣ ከኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲቲዩት እና ከናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንስቲቲዩት የተጣመረው የልዑካን ቡድን የ2013ቱን ምርጫ ሁሉን ያካተተ፣ ግልፅ እና ተጠያቂነትን የተላበሰ ለማድረግ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ቅድሚያ ሰጥተው ሊተገብሯቸው የሚገቡ 12 ምክረ ሃሳቦችን አቅርቧል።”
ተልዕኮው የተካሄደው የኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI) እና የናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንሲቱትዩት (NDI) ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ምርጫ ምዘና ተልዕኮ (International Election Assessment Mission for Ethiopia/IEAME) አንዱ አካል ሆኖ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የምርጫ መታዘቢያ ዘዴን አስተካክሎ በመጠቀም የተከናወነ ነው። ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ምርጫ ምዘና ተልዕኮ (IEAME) ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቀረበለት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የተደራጀ ሲሆን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ታዛቢዎች ሕጎች እና መመሪያዎች መሠረት እውቅና አግኝቷል። የልዑካን ቡድኑ እና የIEAME ዓላማ የቅድመ ምርጫውን ምህዳር ገለልተኛ እና ትክክለኛ ግምገማ ውጤት ለኢትዮጲያውያን እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማቅረብ እና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መመዘኛዎችን መሠረት በማድረግ ከኢትዮጵያ ሕግ ጋር የሚስማሙ ገንቢ ምክረ ሃሳቦችን ማቅረብ ነው። በዓለም የጤና ቀውስ የተነሳ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት የልዑካን ቡድኑ ግምገማውን ያከናወነው ስልታዊ የርቀት ተሳትፎ ዘዴዎችን በመጠቀም ነው። ምርጫ የሕዝባዊ ሉዓላዊነት መገለጫ እንደመሆኑ፣ የምርጫውን ሂደት እና ባህሪ የመገምገም ኃላፊነት በዋንኛነት የኢትዮጵያ ህዝብ ይሆናል፤ በመሆኑም የበለጠ ትርጉም ያለው የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ማንኛውንም አጋጣሚ መጠቀም ይገባል።
በተጨማሪም IEAME ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የተወሰነ የሥራ አመራር ቡድንን፣ ቡድኑን ከርቀት የተቀላቀሉ በልዩ ልዩ ጭብጦች ላይ የረዥም ጊዜ ልምድ እና ዕውቀት ያላቸው ስምንት ባለሞያዎችን እና ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ከፈቀዱ በምርጫው ቀን በቀጥታ የሚገኝ ውስን ቁጥር ያለው ተጨማሪ የቴክኒክ ቡድንን ያካትታል። IEAME እስከ ምርጫው ማጠቃለያ ድረስ የምርጫ ምህዳሩን መተንተኑን የሚቀጥል ሲሆን ከምርጫው በኋላ የመጨረሻ ሪፖርት ያወጣል። IEAME ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስ ኤ አይ ዲ) የገንዘብ ድጋፍ ያገኛል። ሁሉም ተግባሮቹ የሚከናወኑት ገለልተኛ በሆነና ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ወገንተኛነት በሌልበት እንዲሁም በዓለም አቀፍ የምርጫ ምልከታ እና የስነ-ምግባር ደንብ መርሆዎች መግለጫ ድንጋጌዎች መሠረት ነው። ግኝቶቹ እና ምክረ ሃሳቦቹ በሙሉ የናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንሲቱትዩት እና የኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት ብቻ ናቸው።
እ.ኤ.አ. በ1983 ዓ.ም. ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ ናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንሲቱትዩት እና ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት በድምሩ በዓለም ዙሪያ ከ400 በላይ ዓለም አቀፍ የግምገማ እና የምርጫ መታዘብ ተልዕኮዎችን አዘጋጅተዋል፡፡
የጋራ የልዑካን ቡድኑ ሙሉ ሪፖርት ከ NDI እና ከ IRI ድህረ ገፅ ላይ ይገኛል።
ስለ የኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI)፦ በዓለም ዙሪያ ነፃነትን እና ዲሞክራሲን ለማስፋፋት የሚሰራ ገለልተኛ እና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የበለጠ ሃስብን መሠረት ያደረጉ እና ምላሽ ሰጭ እንዲሆኑ ያስችላል፣ ዜጎች በመንግስት እቅድ ውስጥ እንዲሳተፉ ያግዛል እንዲሁም በፖለቲካው ሂደት ውስጥ የተገለሉ ቡድኖች ሚና እንዲጨምር ይሠራል። እ.ኤ.አ. ከ1983 ጀምሮ ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት በ60 ሀገራት ውስጥ 206 ምርጫዎችን በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ተልዕኮዎች እና ግምገማዎች ማካኝነት ተከታትሏል። ለበለጠ መረጃ www.iri.org ጎብኙን።
ስለ ኤን ዲ አይ (NDI)፡– ኤን ዲ አይ የዴሞክራሲ ተቋማትን፣ ሂደቶችን፣ ደንቦችን እና እሴቶችን ለማጠናከር እና ለመጠበቅ እንዲሁም ሁሉም ሰው የተሻለ ጥራት ያለው ኑሮ የሚኖርበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ በዓለም ዙሪያ በአጋርነት የሚሰራ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ መንግስታዊ ያልሆነ እና ከፖለቲካዊ ውግንና ነፃ የሆነ ተቋም ነው። የኤን ዲ አይ ራዕይ ዴሞክራሲ እና ነፃነት የሰፈኑበት እና ሁሉም ሰው ሰብዓዊ ክብሩ የሚጠበቀበት ዓለም ተፈጥሮ ማየት ነው። ላለፉት 38 ዓመታት ኤን ዲ አይ በ70 ሀገራት ውስጥ ከ250 በላይ የምርጫ ታዛቢ ተልእኮዎችን አካሂዷል። ለበለጠ መረጃ ይሚከተለውን ድረ ገፃችንን ይጎብኙ፦ www.ndi.org
###
የማጠቃለያ ግኝቶች እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ምክረ ሃሳቦች
ግንቦት 28 ይካሄዳል ተብሎ ቀን የተቆረጠለት የኢትዮጵያ የ2013 ምርጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎችን መሠረት በማድረግ በአገሪቱ ውስጥ ሁሉን አቀፍ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችል መልካም ዕድል ሊፈጥር ይችላል የሚል ተስፋ አለ። ሆኖም በስፋት የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን እና የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚከናወኑ የእጩዎች እና የመራጮች ምዝገባ ሥነ-ሥርዓቶች ጋር የተያያዙ መዘግየቶችን፣ አንዳንድ የክልል መንግስታት ደካማ የሆነ ትብብር ማሳየታቸውን፣ ስፊ የህዝብ ድጋፍ ያላቸው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ሂደቱ ራሳቸውን ማግለላቸውን እና እናገላለን የሚል ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን፣ እንዲሁም ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን የህዝብ ጤና ቀውስ ጨምሮ አዳጋች የሆኑ የተለያዩ ጉልህ ችግሮች መኖራቸው መራጮች እና ፓርቲዎች በሂደቱ ውስጥ ለመሳተፍ ባላቸው አቅም ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር እና በዚህም ተዓማኒነት ያለው ምርጫ የመከናወኑን ዕድል እንዳያጠበው ያሰጋል። በመሆኑም ከምርጫ ቀን አስቀድሞ በሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚከወኑ ሁነኛ እና የተቀናጁ ጥረቶች ትርጉም ያለው ምርጫ ለማካሄድ እና ከምርጫው ባሻገር ለብሄራዊ እርቅና ለዴሞክራሲያዊ እድገት መሰረት ለመጣል አስፈላጊ ግብአቶች ናቸው።
ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የተተገበሩት የህግ እና የፖለቲካ ማሻሻያዎች ለዜጎች፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ነፃነቶችን ያጎናፀፉ በመሆናቸው መጠነ ሰፊ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ለውጦችን አስከትለዋል። ከምርጫ እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት ባላቸው ሕጎች ላይ የተደረጉ ለውጦች ቀደም ሲል በሕግ ማዕቀፉ ውስጥ የነበሩ በርካታ ገዳቢ ይዘቶችን አስወግደዋል። የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የቦርዱ ሰብሳቢ ሆኖ መሾም ቀደም ሲል የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እና በከፍተኛ ደረጃ የተከበሩ ዳኛ የነበሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የፖለቲካው ማህበረሰብ በአጠቃላይ ለምርጫ ቦርድ የሚሰጠው አክብሮት እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተጨማሪም ምርጫ ቦርድ በሚተዳደርባቸው ሕጎች ላይ የተደረጉ ለውጦች የቦርዱን ድርጅታዊ ነፃነት አሻሽለዋል። ምርጫ ቦርድ በቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን መሪነት ተዓማኒ ምርጫዎችን የማካሄድ አቅሙን ለማጎልበት እና የህዝቡን እምነት ለማትረፍ ረዥም ሂደቱን ጀምሯል። ከምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ በተጨማሪ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ እና የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንቷ ሴት መሆን ሴቶች በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ሊጫወቱት የሚችለውን ወሳኝ ሚና ያሳያል። በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ ተሳትፏቸው ተገድቦ የነበረው የሲቪል ማኅበረሰብ አስተዋጽኦ በስነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት እንዲሁም በምርጫ ሂደት ገለልተኛ ታዛቢ መሆን እንዲችሉ እንደገና ዕድል በመፈጠሩ ሲቪል ማህበራቱ በምርጫ ሂደቱ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መርምሮ መፍታት የሚቻልባቸውን ምክረ ሃሳቦች ማቅረብ ጀምሯል። እነዚህ ተሞክሮዎች ከዚህ ቀደም የነበሩት ሁኔታዎች መቀየራቸውን የሚያሳዩ በመሆናቸው ወሳኝ ናቸው እንዲሁም የበለጠ ሊበረታቱ ይገባል።
ከዚህ ጎን ለጎን በምርጫ ምህዳሩ ውስጥ ያሉ ከባድ እና አሳሳቢ ተግዳሮቶች አሉ። በስፋት ተቃውሞ የገጠማቸው በ1997፣ በ2002 እና በ2007 የተካሄዱት ምርጫዎች እና ከዚያ ጋር ተያይዞ የነበረው የፖለቲካ ጭቆና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችንም ጭምር አቅም ያሰናከለ ሲሆን ይህም እነዚህ አካላት በአሁኑ ወቅት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ላይ የራሱን ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው። ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ከቆዩ የብሔር ውጥረቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው በርካታ የጸጥታ ቀውሶች ያጋጠሟት ሲሆን ይህም በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ በርካታ አካባቢዎች ያለመረጋጋትን ወይም ግልጽ ግጭትን አስከትሏል። የፀጥታ ሁኔታው ህዝቡ በነፃነት እና በንቃት በምርጫ ለመሳተፍ ያለውን ብቃት የሚያዳክም በመሆኑ አንዳንድ ወገኖች ከሂደቱ ራሳቸውን እንዲያገሉ ምክንያት ሆኗል። ግልፅ ግጭት በመኖሩ የተነሳ በትግራይ ክልላዊ መንግስት ምርጫ አይካሄድም። በርካታ ታዋቂ የኦሮሞ የፖለቲካ መሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸው በኢትዮጵያ ትልቁን የሕዝብ ቁጥር በሚይዘው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቅሳቀሱ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ሂደቱ ራሳቸውን በማግለል ተቃውሟቸውን እንዲገልጹ ምክንያት ሆኗል። የፀጥታና የደህንነት አስተማማኝ አለመሆን የሴቶችን፣ የካል ጉዳተኞችን እና የሃገር ውስጥ ተፈናቃይ ዜጎችን የምርጫ ተሳትፎ በተለየ መልኩ ይጎዳል። የሚዲያ ነፃነት ላይ የላቀ መሻሻል የታየ ቢሆንም መደበኛ መገናኛ ብዙሃን አህኑንም በአመዛኙ በመንግስት ደጋፊዎች ድምፆች የበላይነት የተያዙ ናቸው። በተጨማሪም በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ውስጥ ባሉ ግለሰቦች የተሳሳቱ መረጃዎችን ማሰራጨት በስፋት መስተዋሉ የመራጮችን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት ዕድል ያስተጓጉላል። የጥላቻ ንግግሮች መበራከትም የምርጫውን ድባብ አደብዝዞታል። ሴቶች ወደ ከፍተኛ የአመራር ሃላፊነት ቦታዎች መምጣታቸው ሳይጠቀስ የማይታለፍ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ሴቶች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በምርጫ ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ውስን ነው። በስፋት እየተሰራጨ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የማህበረሰቡን የጤና ሁኔታ አስጠብቆ ታማኝነት ያለው ምርጫን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማድረግ ተጨማሪ ፈተና ሆኖ ተጋርጧል። እነዚህ ጉዳዮች የምርጫውን ታማኝነት ስጋት ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው በእጩዎች መረጣ እና በመራጮች ምዝገባ ሂደቶች ላይ ገና ከአሁኑ አሉታዊ ተፅእኖ አሳድረዋል።
ሆኖም ግን ይህ ምርጫ አዎንታዊ እርምጃ ሊሆን እና ወደ ፊት ይበልጥ ተአማኒነት ያላቸው ሂደቶች እንዲኖሩ መሠረት ሆኖ ሊያገለግል የሚችልበት መልካም ዕድል አለ። የልዑካን ቡድኑ ምርጫው ይፋ በተደረገው መሰረት መከናወኑን የሚደግፉ እንዲሁም የሚቃወሙ አካላትን ሃሳብ አድምጧል። ምርጫው የሚደረግበት ጊዜ መቼም ቢሆን የምርጫውን ድባብ ለማሻሻል የተቀናጁ ጥረቶች ያስፈልጋሉ። እስከ ምርጫ ቀን ድረስ ባለው ውስን ጊዜ ውስጥም ቢሆን የ2013 የኢትዮጵያ ምርጫ እንዲሁም ለወደፊቱ የሚደረጉ ምርጫዎች ሀገሪቱን ወደፊት የሚያራምዱ እንዲሆኑ ለማገዝ ኢትዮጵያውያን ሊወስዷቸው እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፋቸው የሚችሉ ወሳኝ እርምጃዎች አሉ። የዴሞክራሲ መስፋፋትን ለማጎልበት ኢትዮጵያውያን ለሚያደረጓቸው ጥረቶች አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት ተስፋ በማድረግ፣ ከኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲቲዩት እና ከናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንስቲቲዩት የተጣመረው የልዑካን ቡድን የ2013ቱን ምርጫ ሁሉን ያካተተ፣ ግልፅ እና ተጠያቂነትን የተላበሰ ለማድረግ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ቅድሚያ ሰጥተው ሊተገብሯቸው የሚገቡ 12 ምክረ ሃሳቦችን አቅርቧል።
ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ምክረ ሃሳቦች
የምርጫን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ
የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ለመራጮች እና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ደህንነቱ የተጠበቀ አከባቢን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። እየተስፋፋ የመጣው አስተማማኝ ያልሆነ የፀጥታ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን በምርጫ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ ሲሆን በተጨማሪም በምርጫ ቀን የሚደረገውን የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንዳያስተጓጉል ያሰጋል። የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ አካላት ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር መራጮችን፣ የምርጫ አስፈፃሚዎችን፣ እጩዎችን፣ ደጋፊዎቻቸውን፣ መራጮች ትምህርት የሚሰጡ ተቋማትን እና ታዛቢዎችን ጨምሮ በመላ አገሪቱ በምርጫው ሂደት ለሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ተሳትፎአቸው ደህንነቱ በተጠበቀ አካባቢ እንዲሆን የፀጥታ ቡድን የማዋቀር እና የማሰማራት ዕቅድ ማዘጋጀት አለባቸው። የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ያለምንም አድሎአዊነት ሥራቸውን ለማከናወን እና በምርጫው አካሄድ ውስጥ ጣልቃ ላለመግባት በይፋ በመወሰን ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት አለባቸው።
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአመፅ፣ ከማስፈራራት እና ከጥላቻ ንግግሮች እራሳቸውን በመቆጠብ በይፋ ለሰላም ጥሪ ማድረግ አለባቸው። የቱንም ያህል በኢትዮጵያ የፖለቲካ በማህበርሰብ ውስጥ ጥልቀት ያላቸው ውዝግቦች ቢኖሩም፣ ሁሉም ዜጎች ያለምንም የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ደህንነታቸው ተጠብቆ በዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ የመሳተፍ ዕድል ሊኖራቸው ይገባል። በምርጫ የሚሳተፉም ሆነ ከምርጫ ሂደቱ እራሳቸውን ያገለሉ ሁሉም ፓርቲዎች በአደባባይ ሁከትን በማውገዝ አገራዊ የሰላም ጥሪ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጥረትን ለመቀነስ በተጠናከረ ሁኔታ ተከታታይ ውይይት ማካሄድ ይኖርባቸዋል። ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሃይል የቀላቀሉ ግጭቶች፣ ማስፈራሪያዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ሥጋቶችን ለማስቀረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ የውይይት መድረኮችን በየጊዜው ሊያመቻች ይገባል። ፓርቲዎች በምርጫ ሥነ ምግባር ደንቦች ለመገዛት ቁርጠኝነታቸውን ሊሲያዩ የሚገባ ሲሆን ደንቡን የሚቃረኑ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ተጠያቂ ማድረግ አለባቸው።
ኢትዮጵያውያን ደህንነታቸው ተጠብቆ በምርጫ ሂደቱ እንዲሳተፉ የኮቪድ-19 የመከላከያ እርምጃዎችን ስልታዊ በሆነ መንገድ መከተል ያስፈልጋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ እስከ ምርጫው ባለው ጊዜ የበለጠ ሊባባስ ይችላል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች ምዝገባ ወቅት ጥቅም ላይ የሚውሉ የደኅንነት ፕሮቶኮሎችን ቢያዘጋጁም፣ የመራጮች በተለይም በገጠር አካባቢዎች እነዚህን መመርያዎች በስፋት የማክበር ጉዳይ ላይ ያለው መረጃ ግልጽ/አስተማማኝ አይደለም። ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅን የተመለከቱ ግልጽ መመሪያዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች በሚደረጉ ቅስቀሳዎች ወቅት እና በምርጫ ጣቢያዎች ተግባራዊ መደረግ አለባቸው፤ ምርጫው በሚከናወንባቸው ስፍራዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ መሆን አለበት፤ እንዲሁም በሚያስፈልገው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሳሙና/የሳኒታይዘር የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መሰራጨት አለባቸው።
የፌዴራል እና የክልል ባለሥልጣናት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሴቶችን የምርጫ ተሳትፎ ለማሳደግ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። ሴቶች ላይ ሊደርስ የሚችል ፆታዊ ጥቃት፣ የፀጥታ መደፍረስ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በቤተሰብ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጫናዎች መኖራቸው፤ እንዲሁም ነባር ማህበራዊ እና ባህላዊ አመለካከቶች ሴቶች በምርጫ ውስጥ ተሳትፎ እንዳያደርጉ እንቅፋት ይፈጥራሉ። የመንግሥትና የምርጫ ተዋንያን እዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ተገቢውን እርምጃ ለመሰድ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን በሚደርጉበት ወቅት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም በተለይ ደግሞ የሥርዓተ-ፆታ ባለሙያዎችን ማካተት አለባቸው። ሴቶች ለድምፅ ሰጪነት እንዲመዘገቡ፣ ድምጽ እንዲሰጡ፣ የምርጫ አስፈፃሚ እንዲሆኑ፣ በእጩነት እንዲሳተፉ፣ የምርጫ ታዛቢዎች እንዲሆኑ እና በአጠቃላይ በምርጫ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ለማበረታታት ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ እና በይፋ መግለጫዎችን ማውጣት ይገባል።
የምርጫ ዝግጅቶች
ለምርጫው የሚደረጉ ዝግጅቶችን ለማጠናከር የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ተቀናጅተው መሥራት እና ለምርጫ ቦርድ ሁሉንም አስፈላጊ ድጋፎች እና ሀብቶች ማቅረብ አለባቸው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል በቂ ድጋፍና ግብዓት ላያገኝ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አሁንም አለ። በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እና በአገራዊ የትብብር መንፈስ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣን አካላት የምርጫውን ሂደት በሁሉም መልኩ ከማደራጀት እና ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ የምርጫ ቦርድን እንዲሁም በክልል እና በምርጫ ክልል ደረጃ ያሉ ጽ/ቤቶቹን ለማገዝ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በሁሉም ሁኔታዎች የመንግስት ባለሥልጣናት በምርጫ ሂደት ሰፊ የመራጮችን እምነት ለማግኘት እንዲቻል በማያዳላ መልኩ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እርምጃ መውሰድ አለባቸው።
በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎችን ጨምሮ ሁሉም ለድምፅ መስጠት ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለመመዝገብ እና ድምጽ ለመስጠት ትርጉም ያለው ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ መደረግ አለበት። ምርጫ ቦርድ ለመራጮች ምዝገባ ሁሉንም የምርጫ ጣቢያዎች ለመክፈት ከፍተኛ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የምዝገባ እና ድምጽ የመስጠት ሂደት ለማስፈፀም ተልእኮ ተሰጥቶታል። ሆኖም በክልል መንግስታት በኩል ያለው ውስን ትብብር የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የምርጫ ጣቢያዎችን ለማቋቋም እና እነኚህ ዜጎች እንዲመዘገቡ ለማስቻል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያለውን እቅድ ተፈፃሚ እንዳያደርግ አግዶታል። የፌዴራል እንዲሁም የክልል መንግስታት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ ለመምረጥ ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በምርጫው ውስጥ ሙሉ በሙሉ መሳተፋቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተደራሽነት መፍጠር አለባቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች ምዝገባ ዙሪያ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዝርዝር መረጃ መስጠት አለበት። የመራጮች ምዝገባ መጠን በአጭር ቀናት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት የብሔራዊ እና የክልል ምዝገባ ቁጥሮች ላይ በከፊል ጥርጣሬ ተፈጥሯል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የበለጠ ለማስረዳት ዝርዝር የምዝገባ መረጃዎችን በመስጠት ከህጉ መስፈርቶች ባሻገር እንዲሄድ እና የህዝብ አመኔታን እንዲያሳድግ ይበረታታል። የሚሰጡት መረጃዎች በቀን፣ በወረዳ፣ በጾታ እና ዕድሜ የተከፋፈሉ መሆን አለባቸው። በተጨማሪም በተደራሽ የምርጫ መረጃ (openelectiondata.net) መርሆዎች መሠረት የመራጮች ዝርዝር ቅጅዎችን በኤሌክትሮኒክ የመልእክት ማተላለፊያ ዘዴ መልክ ማቅረብ ይችላል።
በሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት አማካኝነት ከስነ ዜጋ እና ከመራጮች ትምህርት ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ሥራዎች የፀጥታ ችግር ያለባቸው፣ የመረጃ ተደራሽነት የሌላቸው እና የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን የበለጠ ባካተተ መልኩ ተጠናክረው ሊሰሩ ይገባል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በምርጫው የመሳተፍ ዕድል እንዲኖረው ለማድረግ ተጨማሪ የስነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ጥረቶች ያስፈልጋሉ። የመራጮች ምዝገባ በዘገየባቸው እና የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የስነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ለማህበረሰቡ በአስቸኳይ እንዲዳረስ ያስፈልጋል። በስነ ዜጋ እና በመራጮች ትምህርት አሰጣጡ ሂደትም ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን እና ሌሎች የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማካተት ተጨማሪ ጥረቶች መደረግ አለባቸው።
የመገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊ የምርጫ ሽፋን ለመስጠት እና መረጃ የማጣራት እና የተዛቡ/የሐሰት መረጃዎችን ለመዋጋት በሚያስችል መልኩ የእውነታ ማጣሪያ ስርዓቶችን ለማጠናከር የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለባቸው። በምርጫው ላለመሳተፍ የወሰኑትን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ባሉ የህዝብ መገናናኛ ብዙሃን ፍትሃዊ ሽፋን ማግኘት አለባቸው። የግል መገናኛ ብዙሃንም በተመሳሳይ መልኩ የፖለቲካ አመለካከቶች ብዝሃነትን ጠብቀው መረጃዎችን ለማቅረብ መጣር አለባቸው። የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች እና ጋዜጠኞች የመረጃ ምንጮችን ለማጣራት እና እውነታውን የመፈተሽ ስልቶችን ለማጠናከር ጥረታቸውን በእጥፍ ማሳደግ አለባቸው። ይህም ሂደት ዜጎች የምርጫውን ሂደት እና እጩዎችን በተመለከተ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኙ በማኅበራዊ እና በመደበኛ የመገናኛ ብዙሃን ሚሰራጩ የውሸት መረጃዎችን ለማጋለጥ ያግዛቸዋል።
የምርጫ ቀን እና የድህረ ምርጫ ማግስት
የምርጫ ታዛቢዎች ምርጫውን ለመታዘብ እና ግኝታቸውን ለህዝብ ለማጋራት ያልተገደበ ነፃነት ይፈልጋሉ። ለምርጫ ታዛቢዎች የእውቅና አሰጣጥ አሰራሮች እና መመሪያዎች አግባብ ባልሆነ መልኩ ቢሮክራሲያዊ እና ገዳቢ ናቸው። ገለልተኛ የሆኑ የምርጫ ታዛቢዎች በተለይም ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ የተወጣጡ የዜጎች ታዛቢዎች የሂደቱን ታአማኒነት በመጠበቅ እና ግኝቶቻቸውን በይፋ በማካፈል ዜጎች በምርጫዎች ላይ እምነት እንዲኖራቸው ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእውቅና አሰጣጥ አሰራሮችን ማቀላጠፍና ማፋጠን እንዲሁም ታዛቢዎች ግኝታቸውን በወቅቱ በይፋ እንዲያካፍሉ መፍቀድ አለበት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የውጤት ማቅረቢያ እና ማሳወቅያ ሂደት ሁሉን አቀፍ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ያለፉት የምርጫ ውጤቶች ላይ በሰፊው ይነሱ የነበሩ አለመተማመኖችን በዚህኛው ምርጫ ውቅት ለማስቀረት እንዲቻል ከድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የተገኙ የቆጠራ ውጤቶችን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በፍጥነት እንዲመዘገቡ ማስተላለፍ ያስፈልጋል። የህዝብ አመኔታን ለማሳደግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የውጤት ማሳወቅ ሂደቱ በምን መልኩ እንደሚከናወን ለህዝብ እና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ማስረዳት አለበት። ሁሉንም ስርዓቶች እና የአሰራር ሂደቶች ከምርጫው ቀን በፊት በደንብ መፈተሽ እና ግኝቶቹን ለባለድርሻ አካላት ማጋራት ተገቢ ነው። በውጤቶቹ ላይ ህዝባዊ አመኔታን ለማሳደግ የሁሉም የምርጫ ጣቢያ ውጤቶች በኤሌክትሮኒክ መንገድ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በይነ-መረብ (ኢንተርኔት) ገፅ ላይ በወቅቱ መታተም እና ለህዝብ ይፋ መደረግ አለባቸው።
ከእነዚህ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ምክረ ሃሳቦች ባሻገር የሕግ ማዕቀፉን ለማሳደግ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የበለጠ ለማጠናከር ከምርጫ በኋላ ጉልህ እና የረጅም ጊዜ ጥረቶች ያስፈልጋሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወካይነት ማሳደግ፣ ቀልጣፋ የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎን ማበረታታት፣ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች እና ሌሎች የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የተሟላ ተሳትፎ እንዲኖር ማድረግ እና ሚዛናዊና ትክክለኛ የሆኑ መደበኛ እና ማህበራዊ ሚዲያዎችን የማቅረብ ሂደት ላይ የበለጠ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ ተአማኒነት ያላቸው ምርጫዎች እና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እውን የሚሆኑት የአገሪቱ የፀጥታ ችግሮች ሲፈቱ ነው። ከዚህ አንፃር ታሪካዊ ቅሬታዎችን ትርጉም ባለው መልኩ ለመፍታት ሁሉን አቀፍ አካሄድ መከተል፣ እናም የሀገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ስር የሰደዱ የህብረተሰብ ክፍፍሎችን እና የጎሳ ውጥረቶችን ለመፈወስ ፍትህ እና ብሄራዊ እርቅ እንዲኖር አስፈላጊ ነው።
Top